Boditi millineum tsire Adis kibeb

ዘላቂ ላልሆነ ስራ የሚባክን ጊዜና ሃብት የለንም- ጠ/ሚ ኃይለማርያም
የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በሃገራዊና በአፍሪካ ጉዳዮች ዙሪያ ከ ዘ አፍሪካ ሪፖርት ድረ-ገፅ ጋር ቃለምልልስ አድርገዋል፡፡ ኢትዮጵያ የምትተገብራቸው የልማት እቅዶች የክልል መንግስታትን፤ የግሉን ዘርፍና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ እንደሚቀረፁ ተናግረዋል፡፡ መንግስት በጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመራ ብሄራዊ ምክር ቤት በኩል ሁሉንም የህብረተሰብ አካላት ያካተተ እቅድ መውጣቱን ያረጋግጣል ነው ያሉት፡፡ እቅዶቹን በማውጣት በኩል የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ሚና ቁልፍ ነበርም ብለዋል፡፡ “የምስራቅ ኢስያ ሃገሮችን ልምድ እንደ ምሳሌ ብንወስድ ጠንካራ ራዕይ ያላቸው መሪዎች የሚያሳድሩት አዎንታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህን ራዕይ በሁሉም ዘርፎች በተግባር መፈፀም የህብረተሰቡና የባለሙያዎች ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡ ደቡብ ኮርያና ቻይና ለግሉ ዘርፍ የገበያ ውድድሩን ክፍት ማድረጋቸውን በመጠቆም ኢትዮጵያም ይህን መሰል እቅድ ይኖራት እንደሆነ ለተጠየቁት ሲመልሱ “በርግጥ የቴሌኮም፣ የባንክና ኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎቶቻችን በመንግስት የተያዙ ናቸው፡፡ ይህም ከበስተጀርባው አሳማኝ ኢኮኖሚያዊ ምክንቶች ስላሉት ነው፡፡ ሰዎች የርዕዮተ አለም ጉዳይ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ይህ እውነት አይደለም፡፡ ሁሉም የበለጸጉ አገራት በእድገታቸው መነሻ ጊዜያት ቁልፍ የኢኮኖሚ ተቋሞቻቸውን ወደ ግል አላዞሩም፡፡ አሁን እኛን ወደ ግል እንድናዞር እየነገሩን ቢሆንም ጊዜው ስላልሆነ አናደርገውም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ በሽግግር ኢኮኖሚና በታዳጊነት ውስጥ ባሉ አገራት በርካታ የገበያ ክፍተቶች ስለሚያጋጥሙ መንግስት ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እንዲቻለው የግሉን ዘርፍ መደገፍ አለበት” ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ የኢህአዴግን አመራር ተዋፅዖ አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ኢህአዴግ ከሃገሪቱ አራት ክልሎች ከእያንዳንዳቸው 9 አባላትን ያካተተ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያለው ፓርቲ መሆኑን በመግለጽ ክልሎቹ በድርጅቱ እኩል ውክልና እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡ በፌዴራል ካቢኔውም ሁሉም ክልሎች መወከላቸውን በመጠቆም አሁን ፓርቲው እየተገበረ ያለው የትውልድ ቅብብሎሽን መሰረት ያደረገ የመተካካት ስራ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም በሃገሪቱ እየተካሄደ ያለው የመንደር ማሰባሰብ መርሃ ግብር ኢኮኖሚዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ እንዳለውም ለድረ ገፁ አብራርተዋል፡፡ “ለምሳሌ አንድን ማህበረሰብ በጎጆ ኢንደስትሪዎች ለማሳተፍ ብትፈልግ እዚህና እዚያ ላሉ በቁጥር ሁለት እና ሶስት ሆነው ለተበታተኑ ቤቶች በሙሉ መብራት ማዳረስ አትችልም፡፡ የትምህርት፣ ጤናና የመጠጥ ውሃ አገልግሎቶችን በቀላሉ የማዳረስ ማህበራዊ ጠቀሜታም አለው” ብለዋል፡፡ የመንደር ማሰባሰቡ እየተካሄደ ያለውም በፈቃደኝነት ነው፤ ካልሆነ ግን ሊሳካ እንደማይችል ስለምናውቅ ዘለቄታ ለሌለው ስራ የሚባክን ጊዜና ሃብት የለንም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ፈረንሳይና የምዕራብ አፍሪካ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ በሶማሌ ከነበራት የሠላም ማስከበር ተልዕኮ ምን ሊማሩ ይችላሉ? የሚል ጥያቄም ቀርቦላቸው ነበር፡፡ በማሊ ሊፈጠር ይችል ከነበረው መጥፎ ተጽዕኖና በአካባቢው ላይ ሊኖር ከሚችለው ብጥብጥ አንጻር የፈረንሳይ ሃይል ወደ ማሊ መግባት በጣም አስፈላጊ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ ችግሩን መግታት ከተቻለ በኃላ ግን አሁን አለም አቀፍ ጥረት እንደሚያስፈልግና የፈረንሳይ ብቻ ተልዕኮ ሊሆን እንደማይገባ ነው ጠቅላይ ሚነስትር ኃይለማርያም ያሳሰቡት፡፡ “የአፍሪካ ህብረት በተለይም የቀጠናው ተቋም የሆነው የምዕራብ አፍሪካ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ከሌሎች በላቀ ሊሳተፉበት ይገባል፡፡ ፈረንሳይ ለምዕራብ አፍሪካ ኢኮኖሚ ማህበረሰብና ለአፍሪካ ህብረት በማሊ ጥምር ሃይል ለማቋቋም ያቀረበችው ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል” ብለዋል፡፡ ነገር ግን በማሊ ሠላም ማስጠበቅ ብቻ በቂ አይደለም፤ ዘላቂ ሰላም ሊመጣ የሚችልበትን ስርዓት መፍጠር ይገባል ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፡፡